መዝሙር 57 NASV

በጨካኝ ጠላቶች ዘንድ

ለመዘምራን አለቃ፤ “አታጥፋ” በሚለው ቅኝት የሚዘመር፤ ከሳኦል ፊት ሸሽቶ በዋሻ በነበረበት ጊዜ፤ የዳዊት ቅኔ።

1 ማረኝ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ ማረኝ፤ነፍሴ አንተን መጠጊያ አድርጋለችና፤በክንፎችህ ሥር እጠለላለሁ።

2 ለእኔ ያሰበውን ወደሚፈጽምልኝ አምላክ፣ወደ ልዑል እግዚአብሔር እጮኻለሁ።

3 ከሰማይ ልኮ ያድነኛል፤የረገጡኝን ያዋርዳቸዋል፤ ሴላእግዚአብሔር ምሕረቱንና ታማኝነቱን ይልካል።

4 ነፍሴ በአንበሶች ተከብባለች፤በሚዘነጣጥሉ አራዊት መካከል ወድቄአለሁ፤እነዚህም፣ ጥርሳቸው ጦርና ፍላጻ፣ምላሳቸውም የተሳለ ሰይፍ የሆኑ ሰዎች ናቸው።

5 እግዚአብሔር ሆይ፤ ከሰማያት በላይ ከፍ ከፍ በል፤ክብርህም በምድር ሁሉ ላይ ትስፈን።

6 ለእግሬ ወጥመድን ዘረጉ፤ነፍሴንም አጐበጧት፤በመተላለፊያዬ ላይ ጒድጓድ ቈፈሩ፤ነገር ግን ራሳቸው ገቡበት። ሴላ

7 እግዚአብሔር ሆይ፤ ልቤ ጽኑ ነው፤ልቤ ጽኑ ነው፤እቀኛለሁ፤ አዜማለሁ።

8 ነፍሴ ሆይ፤ ንቂ!በገናና መሰንቆም ተነሡእኔም በማለዳ እነሣለሁ።

9 ጌታ ሆይ፤ በሕዝቦች መካከል አመሰግንሃለሁ፤በሰዎችም መካከል እዘምርልሃለሁ፤

10 ምሕረትህ እስከ ሰማያት ከፍ ብላለችና፤ታማኝነትህም እስከ ደመናት ትደርሳለች።

11 እግዚአብሔር ሆይ፤ ከሰማያት በላይ ከፍ ከፍ በል፤ክብርህም በምድር ሁሉ ላይ ትስፈን።