መዝሙር 35 NASV

የተጨቈነ ሰው ጸሎት

የዳዊት መዝሙር

1 እግዚአብሔር ሆይ፤ የሚታገሉኝን ታገላቸው፤የሚዋጉኝንም ተዋጋቸው።

2 ትልቁንና ትንሹን ጋሻ ያዝ፤እኔንም ለመርዳት ተነሥ።

3 በሚያሳድዱኝ ላይ፣ጦርና ጭሬ ምዘዝ፤ነፍሴንም፣“የማድንሽ እኔ ነኝ” በላት።

4 ሕይወቴን የሚፈልጓት፣ይቅለሉ፣ ይዋረዱ፤እኔን ለማጥፋት የሚያሤሩ፣ዐፍረው ወደ ኋላቸው ይመለሱ።

5 በነፋስ ፊት እንዳለ እብቅ ይሁኑ፤ የእግዚአብሔር መልአክ ያሳዳቸው።

6 መንገዳቸው ጨለማና ድጥ ይሁን፤ የእግዚአብሔር መልአክ ያባራቸው።

7 ያለ ምክንያት ወጥመዳቸውን በስውር አስቀምጠውብኛልና፤ያለ ምክንያት ለነፍሴ ጒድጓድ ቈፍረውላታል።

8 ያልታሰበ ጥፋት ይምጣባቸው፤የሰወሩት ወጥመድ ይያዛቸው፤ይጠፉም ዘንድ ወደ ጒድጓዱ ይውደቁ።

9 ነፍሴም በእግዚአብሔር ደስ ይላታል፤በማዳኑም ሐሤት ታደርጋለች።

10 የሠራ አካላቴ እንዲህ ይልሃል፤“እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ አንተ ማን አለ?ድኻውን ከእርሱ ከሚበረቱ፣ችግረኛውንና ምስኪኑን ከቀማኞች ታድናለህ”።

11 ጨካኝ ምስክሮች ተነሡ፤ስለማላውቀውም ነገር ጠየቁኝ።

12 በበጎ ፈንታ ክፉ መለሱልኝ፤ነፍሴንም ብቸኛ አደረጓት።

13 እኔ ግን እነርሱ በታመሙ ጊዜ ማቅ ለበስሁ፤ነፍሴንም በጾም አደከምኋት፤ጸሎቴም መልስ አጥቶ ወደ ጒያዬ ተመለሰ።

14 ለወዳጄ ወይም ለወንድሜ እንደማደርግ፣እየተንቈራጠጥሁ አለቀስሁ፤ለእናቴም እንደማለቅስ፣በሐዘን ዐንገቴን ደፋሁ።

15 እነርሱ ግን እኔ ስሰናከል በእልልታ ተሰበሰቡ፤ግፈኞች በድንገት ተሰበሰቡብኝ፤ያለ ዕረፍትም ቦጫጨቁኝ።

16 እንደ ምናምንቴዎች አፌዙብኝ፤ጥርሳቸውንም አፋጩብኝ።

17 ጌታ ሆይ፤ እስከ መቼ ዝም ብለህ ታያለህ?ነፍሴን ከክፉ ሥራቸው፣ብርቅ ሕይወቴን ከአንበሶች ታደጋት።

18 በታላቅ ጉባኤ መካከል አመሰግንሃለሁ፤ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበትም አወድስሃለሁ።

19 ከምድር ተነሥተው ጠላቶቼ የሆኑት፣በላዬ ደስ አይበላቸው፤እንዲያው የሚጠሉኝ፣በዐይናቸው አይጣቀሱብኝ።

20 የሰላም ንግግር ከአፋቸው አይወጣም፤ዳሩ ግን በምድሪቱ በጸጥታ በሚኖሩት ላይ፣ነገር ይሸርባሉ።

21 አፋቸውን አስፍተው ከፈቱብኝ፤“ዕሠይ! ዕሠይ! በዐይናችን አየነው” አሉ።

22 እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህን አይተሃልና ዝም አትበል፤ጌታ ሆይ፤ ከእኔ አትራቅ።

23 አምላኬ፣ ጌታዬ፤ ለእኔ ለመሟገት ተነሥ!ልትከራከርልኝም ተንቀሳቀስ።

24 እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ በጽድቅህ ፍረድልኝ፤በእኔም ላይ ደስ አይበላቸው።

25 በልባቸው፣ “ዕሠይ! ያሰብነው ተሳካ!ዋጥ አደረግነውም” አይበሉ።

26 በጭንቀቴ ደስ የሚላቸው፣ይፈሩ፤ ግራም ይጋቡ፤በእኔ ላይ ራሳቸውን ከፍ ከፍ የሚያደርጉ፣ዕፍረትንና ውርደትን ይከናነቡ።

27 ፍትሕ ማግኘቴን የሚወዱ፣እልል ይበሉ፤ ሐሤትም ያድርጉ፤ዘወትርም፣ “የባርያው ሰላም ደስ የሚለው፣ እግዚአብሔር ከፍ ከፍ ይበል!” ይበሉ።

28 አንደበቴ ጽድቅህን፣ምስጋናህንም ቀኑን ሙሉ ይናገራል።