መዝሙር 26 NASV

የንጹሕ ሰው ጸሎት

የዳዊት መዝሙር

1 እግዚአብሔር ሆይ፤ ያለ ነቀፋ እንደ መሆኔ፣አንተው ፍረድልኝ።ወዲያ ወዲህ ሳልልም፣ በእግዚአብሔር ታምኛለሁ።

2 እግዚአብሔር ሆይ፤ ፈትነኝ፤መርምረኝም፤ልቤንና ውስጤን መርምር፤

3 ምሕረትህ ከፊቴ አልተለየምና፣በእውነትህም ተመላለስሁ።

4 ከማይረቡ ጋር አልተቀመጥሁም፤ከግብዞችም ጋር አልተባበርሁም።

5 የክፉዎችን ማኅበር ተጸየፍሁ፤ከዐመፀኞችም ጋር አልቀመጥም።

6 እጆቼን በየዋህነት እታጠባለሁ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ መሠዊያህንም እዞራለሁ፤

7 የምስጋናን ድምፅ አሰማ ዘንድ፣ታምራትህንም አወራ ዘንድ ነው።

8 እግዚአብሔር ሆይ፤ የምትኖርበትን ቤት፣የክብርህን ማደሪያ ቦታ ወደድሁ።

9 ነፍሴን ከኀጢአተኞች ጋር፣ሕይወቴንም ከደም አፍሳሾች ጋር አታስወግዳት።

10 በእነርሱ እጅ የተንኰል ዕቅድ አለ፤ቀኝ እጃቸውም ጒቦን ያጋብሳል።

11 እኔ ግን በተአማኒ ሕይወት እጓዛለሁ፤አድነኝ፤ ምሕረትንም አድርግልኝ።

12 እግሮቼ በደልዳላ ስፍራ ቆመዋል፤በታላቅ ጉባኤ መካከልም እግዚአብሔርን እባርከዋለሁ።