መዝሙር 81 NASV

ለዳስ በዓል የሚዜም ቅኔ

ለመዘምራን አለቃ፤ በዋሽንት የሚዜም፣ የአሳፍ መዝሙር

1 ብርታታችን ለሆነው አምላክ በደስታ ዘምሩ፤ለያዕቆብ አምላክ እልል በሉ።

2 ዝማሬውን ጀምሩ፤ ከበሮውን ምቱ፤በበገናና በመሰንቆ ጥዑም ዜማ አሰሙ።

3 በሙሉ ጨረቃ፣ በክብረ በዓላችን ዕለት፣በወሩ መግቢያ፣ ጨረቃ ስትወለድ መለከት ንፉ፤

4 ይህ ለእስራኤል የተሰጠ ሥርዐት፣የያዕቆብም አምላክ ድንጋጌ ነውና።

5 ሙሉ ለሙሉ ግብፅን ለቆ በወጣ ጊዜ፣ይህን ለዮሴፍ ደነገገለት፤በማላውቀውም ቋንቋ እንዲህ ሲል ሰማሁ፦

6 “ትከሻውን ከሸክም ገላገልሁት፤እጁንም ቅርጫት ከመያዝ አሳረፍሁ።

7 በመከራህ ጊዜ ጠራኸኝ፤ እኔም ታደግሁህ፤በነጐድጓድ መሰወሪያ ውስጥ መለስሁልህ፤በመሪባ ውሃ ዘንድ ፈተንሁህ። ሴላ

8 “ሕዝቤ ሆይ፤ ሳስጠነቅቅህ ስማኝ፤እስራኤል ሆይ፤ ምነው ብታደምጠኝ!

9 በአንተ ዘንድ ባዕድ አምላክ አይኑር፤ለሌላም አምላክ አትስገድ።

10 ከግብፅ ምድር ያወጣሁህ፣እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ነኝ፤አፍህን በሰፊው ክፈተው፤ እኔም እሞላዋለሁ።

11 “ሕዝቤ ግን አላደመጠኝም፤እስራኤልም እጅ አልሰጥ አለኝ።

12 ስለዚህ በገዛ ዕቅዳቸው እንዲሄዱ፣አሳልፌ ለደንዳናው ልባቸው ሰጠኋቸው።

13 “ምነው ሕዝቤ ቢያደምጠኝ ኖሮ፣እስራኤል በመንገዴ በሄደ ኖሮ፣

14 ጠላቶቻቸውን ፈጥኜ ባንበረከክኋቸው ነበር፤እጄን በባላጋራዎቻቸው ላይ ባነሣሁ ነበር።

15 እግዚአብሔርን የሚጠሉ በፊቱ ይርዳሉ፤ቅጣታቸውም እስከ ዘላለም የሚዘልቅ ነው።

16 እናንተን ግን ምርጡን ስንዴ አበላችኋለሁ፤ከዐለቱም ማር አጠግባችኋለሁ።”