መዝሙር 25 NASV

25 የዳዊት መዝሙር

በአደጋ ጊዜ የቀረበ ጸሎት

የዳዊት መዝሙር

1 እግዚአብሔር ሆይ፤ ነፍሴን ወደ አንተ አነሣለሁ፤

2 አምላኬ ሆይ፣ በአንተ እታመናለሁ፤እባክህ አታሳፍረኝ፤ጠላቶቼም አይዘባነኑብኝ።

3 አንተን ተስፋ የሚያደርጉ፣ከቶ አያፍሩም፤ነገር ግን እንዲያው ያለ ምክንያት፣ተንኰለኞች የሆኑ ያፍራሉ።

4 እግዚአብሔር ሆይ፤ አካሄድህን እንዳውቅ አድርገኝ፤መንገድህንም አስተምረኝ።

5 አንተ አዳኜ፣ አምላኬም ነህና፣በእውነትህ ምራኝ፤ አስተምረኝም፤ቀኑን ሙሉ አንተን ተስፋ አድርጌአለሁ።

6 እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህንና ፍቅርህን አስብ፤እነዚህ ከጥንት የነበሩ ናቸውና።

7 የልጅነቴን ኀጢአት፣መተላለፌንም አታስብብኝ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቸርነትህ ብዛት፣እንደ ምሕረትህም መጠን ዐስበኝ።

8 እግዚአብሔር መልካምና ቅን ነው፤ስለዚህ ኀጢአተኞችን በመንገድ ይመራቸዋል።

9 ዝቅ ያሉትን በፍትሕ ይመራቸዋል፤ለትሑታንም መንገዱን ያስተምራቸዋል።

10 ኪዳኑንና ሥርዐቱን ለሚጠብቁ፣ የእግዚአብሔር መንገድ ሁሉ ቸርነትና እውነት ናቸው።

11 እግዚአብሔር ሆይ፤ ኀጢአቴ ታላቅ ነውና፣ስለ ስምህ ይቅር በልልኝ።

12 እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ማን ነው?በተመረጠለት መንገድ ያስተምረዋል።

13 ዘመኑን በተድላ ደስታ ያሳልፋል፤ዘሩም ምድርን ይወርሳል።

14 እግዚአብሔር ምስጢሩን ከሚፈሩት ወዳጆቹ አይሰውርም፤ኪዳኑንም ይገልጥላቸዋል።

15 ዐይኖቼ ሁል ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ናቸው፤እግሮቼን ከወጥመድ የሚያላቅቃቸው እርሱ ነውና።

16 እኔ ብቸኛና የተጨነቅሁ እንደ መሆኔ፣ወደ እኔ ተመለስ፤ ምሕረትም አድርግልኝ።

17 የልቤ መከራ በዝቶአል፤ከጭንቀቴ ገላግለኝ።

18 ጭንቀቴንና መከራዬን ተመልከት፤ኀጢአቴንም ሁሉ ይቅር በለኝ።

19 ጠላቶቼ እንዴት እንደ በዙ ተመልከት፤እንዴት አምርረው እንደሚጠሉኝ እይ።

20 ነፍሴን ጠብቃት፤ ታደገኝም፤መጠጊያዬ ነህና አታሳፍረኝ።

21 አንተን ተስፋ አድርጌአለሁና፣ታማኝነትና ቅንነት ይጠብቁኝ።

22 አምላክ ሆይ፤ እስራኤልን፣ከመከራው ሁሉ አድነው።