1 እግዚአብሔር ሆይ፤አንተ ከትውልድ እስከ ትውልድ መጠጊያችን ሆንህልን።
2 ገና ተራሮች ሳይወለዱ፣ምድርንና ዓለምን ከመፍጠርህ በፊት፣አንተ ከዘላለም እስከ ዘላለም አምላክ ነህ።
3 ሰዎችን ወደ ዐፈር ትመልሳለህ፤“የሰው ልጆች ሆይ፤ ወደ ቦታችሁ ተመለሱ” ትላለህ፤
4 ሺህ ዓመት በፊትህ፣እንዳለፈችው እንደ ትናንት ቀን፣እንደ ሌሊትም እርቦ ነውና።
5 እንደ ጐርፍ ጠርገህ ስትወስዳቸው፣ እንደ ሕልም ይበናሉ፤እንደ ማለዳ ሣር ታድሰው ይበቅላሉ፤
6 ሣሩም ንጋት ላይ አቈጥቍጦ ይለመልማል፤ምሽት ላይ ጠውልጎ ይደርቃል።
7 በቊጣህ አልቀናልና፤በመዓትህም ደንግጠናል።
8 በደላችንን በፊትህ፣የተሰወረ ኀጢአታችንንም በገጽህ ብርሃን ፊት አኖርህ።
9 ዘመናችን ሁሉ በቊጣህ ዐልፎአልና፤ዕድሜአችንንም በመቃተት እንጨርሳለን።
10 የዕድሜአችን ዘመን ሰባ ዓመት፣ ቢበዛም ሰማንያ ነው፤ከዚያ በላይ ከሆነም ድካምና መከራ ብቻ ነው፤ቶሎ ያልፋልና፤ እኛም ወዲያው እንነጒዳለን።
11 የቍጣህን ኀይል ማን ያውቃል?መዓትህም የመፈራትህን ያህል ታላቅ ነው።
12 ጥበብን የተሞላ ልብ ይኖረን ዘንድ፣ዕድሜያችንን መቍጠር አስተምረን።
13 እግዚአብሔር ሆይ፤ ተመለስ፤ ይህ እስከ መቼ ይሆናል?ለአገልጋዮችህም ራራላቸው።
14 በዘመናችን ሁሉ ደስ እንዲለን፣ ሐሤትም እንድናደርግ፣ምሕረትህን በማለዳ አጥግበን።
15 መከራ ባሳየኸን ዘመን መጠን፣ክፉም ባየንባቸው ዓመታት ልክ ደስ አሰኘን።
16 ሥራህ ለአገልጋዮችህ፣ክብርህም ለልጆቻቸው ይገለጥ።
17 የጌታ የአምላካችን ሞገስ በላያችን ይሁን፤የእጆቻችንን ሥራ ፍሬያማ አድርግልን፤አዎን፣ ፍሬያማ አድርግልን።