መዝሙር 145 NASV

ምስጋና ለንጉሡ ለእግዚአብሔር

የዳዊት የምስጋና መዝሙር

1 አምላኬና ንጉሤ ሆይ፤ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ፤ስምህን ከዘላለም እስከ ዘላለም እባርካለሁ።

2 በየቀኑ እባርክሃለሁ፤ስምህንም ከዘላለም እስከ ዘላለም አመሰግናለሁ።

3 እግዚአብሔር ታላቅ ነው፤ እጅግ ሊመሰገንም ይገባዋል፤ታላቅነቱም አይመረመርም።

4 ሥራህን አንዱ ትውልድ ለሌላው ትውልድ ያስተጋባል፤ብርቱ ሥራህን ያውጃል።

5 ስለ ግርማህ ውበትና ክብር ይናገራሉ፤ስለ ድንቅ ሥራህም ያወራሉ።

6 ስለ ድንቅ ሥራህ ብርታት ይነጋገራሉ፤እኔም ስለ ታላቅነትህ ዐውጃለሁ።

7 የበጎነትህን ብዛት በደስታ ያወሳሉ፤ስለ ጽድቅህም በእልልታ ይዘምራሉ።

8 እግዚአብሔር ቸር ነው፤ ርኅሩኅም ነው፤ለቍጣ የዘገየ፣ ምሕረቱ የበዛ።

9 እግዚአብሔር ለሁሉ ቸር ነው፤ምሕረቱም በፍጥረቱ ሁሉ ላይ ነው።

10 እግዚአብሔር ሆይ፤ ፍጥረትህ ሁሉ ያመሰግንሃል፤ቅዱሳንህም ይባርኩሃል።

11 ስለ መንግሥትህ ክብር ይናገራሉ፤ስለ ኀይልህም ይነጋገራሉ፤

12 በዚህም ብርቱ ሥራህን፣የመንግሥትህንም ግርማ ክብር ያስታውቃሉ።

13 መንግሥትህ የዘላለም መንግሥት ናት፤ግዛትህም ለትውልድ ሁሉ ጸንቶ ይኖራል። እግዚአብሔር ቃሉን ሁሉ ይጠብቃል፤በሥራውም ሁሉ ቸር ነው።

14 እግዚአብሔር የሚንገዳገዱትን ሁሉ ይደግፋል፤የወደቁትንም ሁሉ ያነሣል።

15 የሁሉ ዐይን አንተን በተስፋ ይጠብቃል፤አንተም ምግባቸውን በወቅቱ ትሰጣቸዋለህ።

16 አንተ እጅህን ትዘረጋለህ፤የሕያዋን ፍጥረታትንም ሁሉ ፍላጎት ታረካለህ።

17 እግዚአብሔር በመንገዱ ሁሉ ጻድቅ፣በሥራውም ሁሉ ቸር ነው።

18 እግዚአብሔር ለሚጠሩት ሁሉ፣በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው።

19 ለሚፈሩት ፍላጎታቸውን ይፈጽማል፤ጩኸታቸውን ይሰማል፤ ያድናቸዋልም።

20 እግዚአብሔር የሚወዱትን ሁሉ ይጠብቃል፤ክፉዎችን ሁሉ ግን ያጠፋል።

21 አፌ የእግዚአብሔርን ምስጋና ይናገራል፤ፍጡር ሁሉ ከዘላለም እስከ ዘላለም፣ ቅዱስ ስሙን ይባርክ።