መዝሙር 75 NASV

ለመለኮታዊው ዳኛ የቀረበ ዝማሬ

ለመዘምራን አለቃ፤ “አታጥፋ” በሚለው ቅኝት የሚዜም፤ የአሳፍ መዝሙር ማሕሌት

1 አምላክ ሆይ፤ ምስጋና እናቀርብልሃለን፤ስምህ ቅርብ ነውና ምስጋና እናቀርብልሃለን፤ሰዎችም ስለ ድንቅ ሥራህ ይናገራሉ።

2 አንተም እንዲህ አልህ፤ “ለይቼ በወሰንኋት ሰዓት፣በቅን የምፈርድ እኔ ነኝ።

3 ምድርና ሕዝቦቿ ሁሉ በሚናወጡበት ጊዜ፣ምሰሶቿን አጽንቼ የምይዝ እኔ ነኝ። ሴላ

4 እብሪተኛውን፣ ‘አትደንፋ’፤ክፉውንም ‘ቀንድህን ከፍ አታድርግ እለዋለሁ፤

5 ቀንድህን ወደ ሰማይ አታንሣ፤ዐንገትህንም መዝዘህ አትናገር።’ ”

6 ክብር ከምሥራቅ ወይም ከምዕራብ፣ወይም ከምድረ በዳ አይመጣምና፤

7 ነገር ግን የሚፈርድ እግዚአብሔር ነው፤እርሱ አንዱን ዝቅ፣ ሌላውን ከፍ ያደርጋል።

8 በእግዚአብሔር እጅ ጽዋ አለ፤በሚገባ የተቀመመና ዐረፋ የሚወጣው የወይን ጠጅ ሞልቶበታል፤ይህን ከውስጡ ወደ ውጭ ገለበጠው፤የምድር ዐመፀኞችም አተላው ሳይቀር ይጨልጡታል።

9 እኔ ግን ይህን ለዘላለም ዐውጃለሁ፤ለያዕቆብም አምላክ ዝማሬ አቀርባለሁ።

10 የክፉዎችን ሁሉ ቀንድ እሰብራለሁ፤የጻድቃን ቀንድ ግን ከፍ ከፍ ይላል።