መዝሙር

ምዕራፎች 30

መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ከክፉ አደጋ የዳነ ሰው ምስጋና

ለቤተ መቅደሱ ምረቃ የተዘመረ፤ የዳዊት መዝሙር

1 እግዚአብሔር ሆይ፤ ከታች አንሥተኸኛልና፣ጠላቶቼም በላዬ እንዳይደሰቱ አድርገሃልና፣ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ። 2 እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ ትረዳኝ ዘንድ ወደ አንተ ጮኽሁ፤አንተም ፈወስኸኝ። 3 እግዚአብሔር ሆይ ነፍሴን ከሲኦል አወጣሃት፤ወደ ጒድጓድ ከመውረድም መልሰህ ሕያው አደረግኸኝ። 4እናንተ ቅዱሳኑ፤ ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ቅዱስ ስሙንም አወድሱ። 5ቊጣው ለዐጭር ጊዜ ነው፤ቸርነቱ ግን እስከ ዕድሜ ልክ ነውና፤ሌሊቱን በልቅሶ ቢታደርም፣በማለዳ ደስታ ይመጣል። 6እኔም በተረጋጋሁ ጊዜ፣“ከቶ አልናወጥም” አልሁ። 7 እግዚአብሔር ሆይ፤ በአንተ ሞገስ፣ተራሮቼ ጸኑ፣ፊትህን በሰወርህ ጊዜ ግን፣ውስጤ ታወከ። 8 እግዚአብሔር ሆይ፤ ወደ አንተ ተጣራሁ፤ወደ ጌታም እንዲህ ብዬ ጮኽሁ፤ 9“በእኔ ወደ ጒድጓድ መውረድ፣በመሞቴ ምን ጥቅም ይገኛል?ዐፈር ያመሰግንሃልን?ታማኝነትህንስ ይናገራልን? 10 እግዚአብሔር ሆይ፤ ስማ፤ ማረኝም፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ ረዳት ሁነኝ።” 11ዋይታዬን ወደ ሽብሸባ ለወጥህልኝ፤ማቄን አውልቀህ ፍስሓን አለበስኸኝ፤ 12እንግዲህ ነፍሴ ታመስግንህ፤ ዝምም አትበል፤ እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ ለዘላለም አመሰግንሃለሁ።