1 እግዚአብሔር ሆይ፤ በፍጹም ልቤ አመሰግንሃለሁ፤ስለ ድንቅ ሥራዎችህም ሁሉ እናገራለሁ።
2 በአንተ ደስ ይለኛል፤ ሐሤትም አደርጋለሁ፤ልዑል ሆይ፤ ስምህን በመዝሙር እወድሳለሁ።
3 ጠላቶቼ ወደ ኋላ በተመለሱ ጊዜ፣ተሰነካክለው ከፊትህ ይጠፋሉ፤
4 ፍርዴም ጒዳዬም በአንተ እጅ ናቸውና፤ቅን ፍርድ እየሰጠህ በዙፋንህ ላይ ተቀምጠሃል።
5 ሕዝቦችን ገሠጽህ፤ ክፉዎችንም አጠፋህ፤ስማቸውንም እስከ ወዲያኛው ደመሰስህ።
6 ጠላቶች ለዘላለም ጠፉ፤ከተሞቻቸውንም ገለባበጥሃቸው፤መታሰቢያቸውም ተደምስሶአል።
7 እግዚአብሔር ግን ለዘላለም በዙፋኑ ላይ ነው፤መንበሩንም ለፍርድ አጽንቶአል።
8 ዓለምን በጽድቅ ይዳኛል፤ሕዝቦችንም በፍትሕ ይገዛል።
9 እግዚአብሔር ለተጨቈኑት ዐምባ ነው፤በመከራም ጊዜ መጠጊያ ይሆናቸዋል።
10 ስምህን የሚያውቁ ይታመኑብሃል፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ የሚሹህን አትተዋቸውምና።
11 በጽዮን ለሚኖር ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ሥራውንም በሕዝቦች መካከል በግልጽ አውሩ፤
12 ደም ተበቃዩ ዐስቦአቸዋልና፤የጭቍኖችንም ጩኸት አልዘነጋም።
13 እግዚአብሔር ሆይ፤ ጠላቶቼ የሚያደርሱብኝን መከራ ተመልከት፤አይተህም ራራልኝ፤ ከሞት ደጅም አንሥተህ መልሰኝ፤
14 ይህን ስታደርግልኝ፣ በጽዮን ሴት ልጅ ደጅ፣ምስጋናህን ዐውጃለሁ፤በማዳንህም ሐሤት አደርጋለሁ።
15 አሕዛብ በቈፈሩት ጒድጓድ ገቡ፤እግራቸውም ራሳቸው በስውር ባስቀመጡት ወጥመድ ተያዘ።
16 እግዚአብሔር በትክክለኛ ፍርዱ የታወቀ ነው፤ክፉዎችም በእጃቸው ሥራ ተጠመዱ። ሒጋዮን ሴላ
17 ክፉዎች ተመልሰው ወደ ሲኦል ይወርዳሉ፤እግዚአብሔርን የሚዘነጉ ሕዝቦችም ሁሉ እንደዚሁ።
18 ችግረኞች ግን መቼም ቢሆን አይረሱም፤የድኾችም ተስፋ ለዘላለም መና ሆኖ አይቀርም።
19 እግዚአብሔር ሆይ ተነሥ፤ ሰውም አያይል፤አሕዛብም በፊትህ ይፈረድባቸው።
20 እግዚአብሔር ሆይ፤ ድንጋጤ አምጣባቸው፤ሕዝቦች ሰው ከመሆን እንደማያልፉ ይወቁ። ሴላ