14 ፍላጻውን አስፈንጥሮ በተናቸው፤መብረቅ አዥጐድጒዶ አሳደዳቸው።
15 እግዚአብሔር ሆይ፤ ከተግሣጽህ የተነሣ፣ከአፍንጫህም እስትንፋስ የተነሣ፣የባሕር ወለል ተገለጠ፤የዓለምም መሠረት ራቍቱን ቀረ።
16 ከላይ እጁን ወደ ታች ዘርግቶ ያዘኝ፤ከብዙ ጥልቅ ውሃም አወጣኝ፤
17 ከኀያላን ጠላቶቼ አዳነኝ፤ከእኔ ከሚበረቱ ባላንጣዎቼም ታደገኝ።
18 እነርሱ በመከራዬ ቀን መጡብኝ፤ እግዚአብሔር ግን ድጋፍ ሆነኝ።
19 ወደ ሰፊ ስፍራ አወጣኝ፤ደስ ተሰኝቶብኛልና አዳነኝ።
20 እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ መልሶልኛል፤እንደ እጄ ንጽሕናም ከፍሎኛል፤