1 ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፤የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያውጃሉ።
2 ቀን ለሌላው ቀን ይናገራል፤ሌሊትም ለሌሊት ዕውቀትን ይገልጣል፤
3 ንግግር የለም፤ ቃል የለም፤ድምፃቸው በጆሮ የሚሰማ አይደለም።
4 ያም ሆኖ ድምፃቸው ወደ ምድር ሁሉ፣ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ይወጣል።እርሱ በሰማያት ለፀሓይ ድንኳን ተክሎአል፤
5 ፀሓይም ከእልፍኙ እንደሚወጣ ሙሽራ ይወጣል፤ወደ ግቡም እንደሚሮጥ ብርቱ ሰው ደስ ይለዋል።
6 መውጫው ከሰማያት ዳርቻ ነው፤ዑደቱም እስከ ሌላኛው ዳርቻ ነው፤ከትኩሳቱም የሚሰወር የለም።
7 የእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ነው፤ነፍስንም መልሶ ያለመልማል፤ የእግዚአብሔር ሥርዐት የታመነ ነው፤አላዋቂውን ጥበበኛ ያደርጋል።