1 ልቤ መልካም ሐሳብ አፈለቀ፤የተቀኘሁትን ቅኔ ለንጉሥ አሰማለሁ፤አንደበቴም እንደ ባለ ሙያ ጸሓፊ ብርዕ ነው።
2 አንተ ከሰዎች ሁሉ ይልቅ ውብ ነህ፤ከንፈሮችህም የጸጋ ቃል ያፈልቃሉ፤ስለዚህ እግዚአብሔር ለዘላለም ባርኮሃል።
3 ኀያል ሆይ፤ ሰይፍህን በወገብህ ታጠቅ፤ግርማ ሞገስንም ተላበስ።
4 ስለ እውነት፣ ስለ ትሕትና ስለ ጽድቅ፣ሞገስን ተጐናጽፈህ በድል አድራጊነት ገሥግሥ፤ቀኝ እጅህም ድንቅ ተግባር ታሳይ።
5 የሾሉ ፍላጻዎችህ በንጉሥ ጠላቶች ልብ ይሰካሉ፤ሕዝቦችም ከእግርህ በታች ይወድቃሉ።
6 አምላክ ሆይ፤ ዙፋንህ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይኖራል፤የመንግሥትህ በትር የቅንነት በትር ናት።