1 ኀያሉ አምላክ፣ እግዚአብሔር ተናገረ፤ከፀሓይ መውጫ እስከ ፀሓይ መግቢያ ድረስ ምድርን ጠራት።
2 ፍጹም ውብ ከሆነችው ከጽዮን፣እግዚአብሔር አበራ።
3 አምላካችን ይመጣል፤ ዝምም አይልም፤የሚባላ እሳት በፊቱ፣የሚያስፈራ ዐውሎ ነፋስም በዙሪያው አለ።
4 በሕዝቡ ይፈርድ ዘንድ፣በላይ ያለውን ሰማይንና ምድርን እንዲህ ብሎ ይጠራል፤
5 “በመሥዋዕት ከእኔ ጋር ኪዳን የገቡትን፣ቅዱሳኔን ወደ እኔ ሰብስቧቸው።”
6 ሰማያት ጽድቁን ያውጃሉ፤እግዚአብሔር ራሱ ፈራጅ ነውና። ሴላ
7 “ሕዝቤ ሆይ፤ ስማኝ፤ ልንገርህ፤እስራኤል ሆይ፤ በአንተ ላይ ልመስክር፤አምላክህ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።