5 የሲኦል ገመድ ተጠመጠመብኝ፤የሞት ወጥመድም ተጋረጠብኝ።
6 በተጨነቅሁ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፤እንዲረዳኝም ወደ አምላኬ ጮኽሁ፤እርሱም ከመቅደሱ ድምፄን ሰማ፤ጩኸቴም ከፊቱ ደረሰ፤ ወደ ጆሮውም ገባ።
7 ምድር ተንቀጠቀጠች፤ ተናወጠችም፤የተራሮችም መሠረት ተናጋ፤ጌታ ተቈጥቶአልና ተንቀጠቀጡ።
8 ከአፍንጫው ጢስ ወጣ፤የሚባላ እሳት ከአፉ፤የፍም ነበልባል ከእርሱ ፈለቀ።
9 ሰማያትን ሰንጥቆ ወረደ፤ከእግሩም በታች ጥቍር ደመና ነበረ።
10 በኪሩቤል ላይ ተቀምጦ በረረ፤በነፋስም ክንፍ መጠቀ።
11 ጨለማን መሰወሪያው፣ በዙሪያውም አጐበሩ አደረገው፤በዝናብ አዘል ጥቍር ደመናም ተሸፈነ።