1 እናንተ ሕዝቦች ሁላችሁ፤ ይህን ስሙ፤በዓለም የምትኖሩ ሁሉ፤ ይህን አድምጡ።
2 ዝቅተኞችና ከፍተኞች፤ባለጠጎችና ድኾች ይህን በአንድነት ስሙ።
3 አፌ የጥበብን ቃል ይናገራል፤የልቤም ሐሳብ ማስተዋልን ይሰጣል።
4 ጆሮዬን ወደ ምሳሌ አዘነብላለሁ፤እንቆቅልሼንም በበገና እፈታለሁ።
5 የአጭበርባሪዎች ክፋት በከበበኝ ጊዜ፣በክፉ ቀን ለምን እፈራለሁ?
6 በሀብታቸው የሚመኩትን፣በብልጽግናቸውም የሚታመኑትን ለምን እፈራለሁ?
7 የሌላውን ሕይወት መቤዠት የሚችል ሰው፣ወይም ለእግዚአብሔር ወጆ የሚከፍልለት ማንም የለም።
8 የነፍስ ቤዛ ውድ ነውና፤በቂ ዋጋም ከቶ ሊገኝለት አይችልም፤
9 በዚህም ዘላለም ይኖራል፣መበስበስንም አያይም።
10 ጠቢባን ሟች መሆናቸው የሚታይ ነው፤ቂልና ሞኝም በአንድነት ይጠፋሉ፤ጥሪታቸውንም ለሌላው ጥለው ይሄዳሉ።
11 መሬቶችን በስማቸው ቢሰይሙም፣መቃብራቸው የዘላለም ቤታቸው፣ከትውልድ እስከ ትውልድም መኖሪያቸው ይሆናል።
12 ሰው በሀብቱ እንደ ተከበረ አይዘልቅም፤ታይተው የሚጠፉ እንስሳትን ይመስላል።
13 ይህ የተላላዎች ዕድል ፈንታ፣የእነርሱንም አባባል ተቀብለው ለሚከተሏቸው፣መጨረሻ ግብ ነው። ሴላ
14 እንደ በጎች ለሲኦል የተዳረጉ ናቸው፤ሞትም እረኛቸው ይሆናል፤ቅኖች በማለዳ ይገዟቸዋል፤አካላቸው ከክብር ቤታቸው ርቆ፣በሲኦል ይፈራርሳል።
15 እግዚአብሔር ግን ነፍሴን ከሲኦል እጅ ይቤዣታል፤በርግጥም በእርሱ ዘንድ ተቀባይነት አለኝ። ሴላ
16 ሰው ባለጠጋ ሲሆን፣የቤቱም ክብር ሲበዛለት አትፍራ፤
17 በሚሞትበትም ጊዜ ይዞት የሚሄደው አንዳች የለምና፤ክብሩም አብሮት አይወርድም።
18 በሕይወት ሳለ ራሱን እንደ ተባረከ ቢቈጥርም፣ሰዎች በበለጸግህ ጊዜ ቢያወድሱህም፣
19 ብርሃን ከቶ ወደማያዩት፣ወደ አባቶች ማኅበር ይቀላቀላል።
20 ሰው በሀብቱ እንደ ተከበረ አይዘልቅም፤ታይተው የሚጠፉ እንስሳትን ይመስላል።