2 እግዚአብሔር ዐለቴ፣ መጠጊያዬና ታዳጊዬ ነው፤አምላኬ የምሸሸግበት ዐለቴ፤እርሱ ጋሻዬ፣ የድነቴ ቀንድና ዐምባዬ ነው።
3 ምስጋና የሚገባውን እግዚአብሔርን እጠራለሁ፤ከጠላቶቼም እድናለሁ።
4 የሞት ገመድ አነቀኝ፤የጥፋት ጐርፍም አጥለቀለቀኝ።
5 የሲኦል ገመድ ተጠመጠመብኝ፤የሞት ወጥመድም ተጋረጠብኝ።
6 በተጨነቅሁ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፤እንዲረዳኝም ወደ አምላኬ ጮኽሁ፤እርሱም ከመቅደሱ ድምፄን ሰማ፤ጩኸቴም ከፊቱ ደረሰ፤ ወደ ጆሮውም ገባ።
7 ምድር ተንቀጠቀጠች፤ ተናወጠችም፤የተራሮችም መሠረት ተናጋ፤ጌታ ተቈጥቶአልና ተንቀጠቀጡ።
8 ከአፍንጫው ጢስ ወጣ፤የሚባላ እሳት ከአፉ፤የፍም ነበልባል ከእርሱ ፈለቀ።